ዶ/ር ዘመዱ ወርቁ መሸሻ ከአባታቸው ከባሻ ወርቁ መሸሻ እና ከእናታቸው እማሆይ ከበቡሽ ጐዳና በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ፍልውሃ በሚባለው አካባቢ በ1925 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በበየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ከጨረሱ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ ፖይንት ፎር (Point Four) በሚባል ከሚታወቀው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የነፃ ትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) በማግኘት ጅማ በሚገኘው የእርሻ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ፡፡ በመቀጠልም ዓለማያ እርሻ ኮሌጅ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡
ከዚያም ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ወደ አሜረካ በማቅናት የማስትሬት ዲግሪያቸውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሃዋይ፣ የፒ.ኤች.ዲ (ዶክትሬት) ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ የዶክትሬት ምርምራቸውም በቃሪያ ላይ ሲሆን ወደ አገር ከተመለሱም በኋላ በርዕሰ ጉዳዩ አያሌ ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡ በተለይም ፋና ለተባሉ ወዳጃቸው ዘር ሰጥተዋቸው የተሰራጨው ማረቆ ፋና የተባለው ዝርያ ከፍተኛ ታዋቂነትን ለማግኘት ችሏል፡፡
ከዚያ በኋላ የቀሰሙትን ትምህርት ለሀገራቸው ዕድገት ለማዋል ባላቸው ቁርጠኝነት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት እና በልዩ ልዩ የአካዳሚክ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም በደብረ ዘይት የእርሻ ምርምር ኢንስቲቱት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው አመራር ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የዕድገት በኀብረት ዘመቻ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት መሪና አስተባባሪ በመሆን ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ያሳዩትን የአመራር ብቃት፣ የመግባባትና የማግባባት ችሎታ እና ለዘማቾች ያደርጉት የነበረውን እንክብካቤ በስራቸው ተሰማርተው የነበሩት ዘማቾች እስካሁንም የሚያስታውሱት ነው፡፡
ከዚያ በኋላ በደረሰባቸው የፖለቲካ ጫና ከሀገር ለመሰደድ ተገደው ለአያሌ ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ተጠሪ በመሆን በተለያዩ አፍሪካ እና ካሪቢያን አገራት አመራር ሰጥተዋል፡፡ እነዚህም አገራት ላይቤሪያ፣ የካሪቢያን ደሴቶች (ጃሜይካ፣ ሴይንት ኪትስ፣ ትሪኒዳድ እና ቶቤጎ፣ ዶሚኒካን ሬፑብሊክ እና ሴይንት ቪንሰንትና ግሬናዳ)፣ እና ኬንያ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ሮም ወደሚገኘው የፋኦ ዋና መሥሪያ ቤት በመዛወር ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1985 ድረስ እዚያ ሠርተዋል፡፡
አገራቸው ከተመለሱ በኋላም በአገር ጉዳይ ዕውቀታቸውን እና ልምዳቸውን ለማካፈል ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (በዚያን ጊዜ አጠራሩ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ) በ1990 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመሪያው ቦርድ አባል እንዲሆኑ ሲጠየቁ ያለምንም ማመንታት ፈቃደኛነታቸውን የገለፁት፡፡ በዚህም በሁለት ዙር ስምንት ዓመታት በዘለቀው ኃላፊነታቸው በቦርድ ስብሰባዎች ላይ ሳያፋልሱ በመገኘት ገንቢ ሐሳቦች ከማቅረባቸውም በላይ፤ መድረኩ በሚያደርጋቸው አያሌ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ በአወያይነት፣ በጽሑፍ አቅራቢነት እና አስተያየት በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ በአጠቃላይ ከመድረኩ ቦርድ አባላት፣ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ከፍተኛ ፍቅርና ከበሬታ ለማግኘት በቅተዋል፡፡
ዶ/ር ዘመዱ ምንም እንኳን ከአብራካቸው የወጣ ልጅ ባይኖራቸውም፤ በርካታ ልጆችን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ለከፍተኛ ማዕረግ አብቅተዋል፡፡ ዶ/ር ዘመዱ ስማቸውን የኖሩ፣ ለዘመድ ደራሽ በመሆን የብዙዎችን ችግር የቀረፉ፣ ከዘመድም አልፈው ልግስናቸውንና ርኅራኄያቸውን ለብዙ ሰዎች የቸሩ ደግ ሰው ነበሩ፡፡ ከዚያም አልፎ ወዳጅነታቸው የፀናና የማያወላውል ነበር፡፡ ለዚህም አንድ ጥሩ ማስረጃ መጀመሪያ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ከተገናኗቸው ሦስት ጓደኞቻቸው ጋር ዘመናትን ተሻግሮ (ጂማ፣ ዓለማያ፣ ስደት፣ ወዘተ) እስካሁን የዘለቀው ወዳጅነት ነው፡፡
ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ጤናቸው እየታወከ መጥቶ በቅርቡ ደግሞ እየጠነከረባቸው ስለሄደ፤ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ታኅሣሥ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ታኅሣሥ 7 ቀን በቱሉ ዲምቱ ደብረ ሠላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡
ለሀገር ለወገን እና ለፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ያበረከቱት አገልግሎት ግን ከመቃብራቸው በላይ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡



